Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ለመምህራን የሰጡት እውቅና ይበልጥ እንድንሰራ የሚያበረታታ ነው – ማህበሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መምህራን በትውልድ ግንባታ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የሰጡት እውቅና ይበልጥ እንድንሰራ የሚያበረታታ ነው ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም÷ኢትዮጵያን ከሚያስቀጥሉ ምሰሶዎች መካከል አርሶ አደር፣ ወታደርና መምህር ወሳኝ ናቸው ፤በመሆኑም ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ መምህርን ማሕበር ፕሬዚዳንት ዩሐንስ በንቲ (ዶ/ር)÷ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምህራን የሰጡት እውቅና ትውልድን የመቅረጽ ተግባራችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ተነሳሽነት የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት የሰጡት እውቅና ህብረተሰቡ ለመምህራን ዘወትር ክብር መስጠት እንዳለበት የሚያስገነዝብ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ሁሌም ሀገርና ትውልድን አስቀድመው እንደሚሰሩ አውስተው÷ኢትዮጵያ ለዘመናት ባለፈችባቸው የትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥም ትልቁን ሚና እንደሚይዙ ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ይህንን ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው÷ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ አግባብ መንግስት ለመመለስ እንደሚሰራ መግለጻቸውንም አድንቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.