በአውሮፓ ዋንጫ ጀርመንና ስፔን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር አዘጋጇ ጀርመን ከስፔን ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
በዚህ መሰረትም አዘጋጇ ጀርመን እና ስፔን ምሽት 1 ሰዓት ላይ በስቱትጋርት አሬና ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
የአውሮፓ ዋንጫ አዘጋጇ ጀርመን ዴንማርክን፤ ስፔን ደግሞ ጆርጂያን በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜው ማለፋቸው ይታወቃል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የሚያደርጉት ትንቅንቅም በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ጀርመን እና ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን በተመሳሳይ ሶስት ሶስት ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ ሀገራት መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በተጨማሪም ፖርቹጋል እና ፈረንሳይ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ምሽት 4 ሰዓት ላይ በቮልክስፓርክ ስታዲየም ያደርጋሉ፡፡
በጥሎ ማለፉ ፖርቹጋል ስሎቬኒያን እንዲሁም ፈረንሳይ ቤልጂየምን በማሸነፍ ነው ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀሉት፡፡
በጨዋታው ከዋክብቶቹ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ኪሊያን ምባፔ ሀገራቸውን ወደ ግምሽ ፍጻሜው ለማሳለፍ የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ነው፡፡