በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ሃይሎች አብዛኛዎቹ ወደ ሰላም መምጣታቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቡድኖች አብዛኛዎቹ ወደ ሰላም ፊታቸውን አዙረዋል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ከብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በቅድመ-ዝግጅት ስራዎች በተሻለ የመፈጸም አቅምና ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነር ተመስገን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ዙር የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የስልጠና ሰነዶች ዝግጅት፣ የማዕከላት ልየታ፣ የምዝገባ መተግበሪያ ማበልጸግና የቅድመ-ሙከራ ስራዎች፣ እንዲሁም በሳይኮ-ሶሻልና ሲቪክስ ሰነዶች ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው÷ በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች አብዛኛዎቹ ከመንግስት ጋር በመስማማት ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡
ትጥቅ በመፍታት ወደ ሰላም የመጡትን የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ኮሚሽኑ ክልሉ የጀመረውን ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት የመመለስ ስራ እንደሚያግዝ መግለፁን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡