ፍርድ ቤቱ የሰበር ውሳኔ የድምጽ ቅጂ ለኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር አበረከተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠባቸውን በድምጽ ቅጂ መልክ የተዘጋጁ የሰበር ውሳኔዎች ለኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር አበርክቷል፡፡
የድምጽ ቅጂው የተዘጋጀው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ተደራሽ የሚያደርጋቸውን በሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡና አስገዳጅነት ያላቸውን ውሳኔዎች በተለየ ሁኔታ ለአይነስውራን ተደራሽ ለማድረግና አማራጮችን በማስፋት አጠቃላይ ተገልጋዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት÷ ለማህበሩ በድምጽ ቅጂ መልክ የተዘጋጁ የሰበር ውሳኔዎችን ማበርከቱ ከፍላጎት ባለፈ የፍርድ ቤቱ ሃላፊነት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም የሰበር ውሳኔዎች ለማህበሩ ተደራሽ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡
አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ በመገንዘብ ይበልጥ ተቋማቱን በማቀራረብ በትብብር ለመስራት ያግዛሉ ብለዋል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በበኩላቸው÷ የዓይነ ስውራን ማህበርን ከተቋማት ጋር በሚኖሩ የጋራ መድረኮች ላይ በማሳተፍ ግብአቶችን ለማሰባሰብ የሚረዳ ስራ የሚሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የዛሬው መልካም ጅማሮም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የዓይነ ስውራን ማህበር ፕሬዚዳንት አበራ ረታ÷ ለዓይነስውራን ለተዘጋጀው ቅጂ ፍርድ ቤቱን አመስግነው፤ ቅጾቹ በድምጽ ቅጂ መልክ ተደራሽ በመሆናቸው ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸው፤ ለማስተማሪያ ግብዓትነት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድምጽ ቅጂዎችን ማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች በፍርድ ቤቱ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች መውሰድ እንደሚችሉም ተጠቁሟል።