የ65 ዓመቱ አዛውንት ለ12ኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት….
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታታሪው የ65 ዓመቱ የጥበቃ ሠራተኛ በቀለ መንጋ ዘንድሮ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ከሚወስዱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ሰውዬው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን አብራሞ ወረዳ የመገሌ-34 ቀበሌ ነዋሪና የአሶሳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጥበቃ ሠራተኛ ናቸው፡፡
ከሥራቸው ጎን ለጎን ትምህርታቸውን በትጋት እየተከታሉ 12ኛ ክፍል መድረሳቸውን የሚናገሩት አቶ በቀለ÷ ዘንድሮ በኦንላይን የሚሰጠውን ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ እየተሰናዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
የኮምፒውተር ዕውቀት የኑሮ ዘይቤን በማቅለል ረገድ ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ወጣቶች በአግባቡ እንዲያውቁትና እንዲረዱት መምከራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጠንክረው ማጥናታቸውን ጠቅሰው÷ “ፈጣሪ ከረዳኝና በጥረቴ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካገኘሁ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ፍላጎት አለኝ” ይላሉ፡፡
ትምህርት በዕድሜ እንደማይገደብ በ65 ዓመቴ የ12ኛ ክፍል ተማሪ መሆኔ ማሳያ ነው፤ ይህም የ10ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪ ልጆቼ እና ሌሎችም እንዲበረቱ በአርዓያነት የሚታይ ነው ብለዋል፡፡
የጥበቃ ሥራቸውን ወደ ተሻለ የሙያ ዘርፍ ለማሣደግ ተስፋ መሠነቃቸውን እና በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የማኅበራዊ ሣይንስ ዘርፍ ተፈታኝ መሆናቸውንም ያብራራሉ፡፡
“ዕድሜዬ ቢገፋም ከጥበቃ ሥራዬ ጎን ለጎን ትምህርቴን በመከታተሌ ደስተኛ ነኝ፤ በቀጣይም የመማር ፍላጎቴን ለማሳካት እጥራለሁ” ሲሉም አመላክተዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሐመድ ኡስማንና የአሶሳ 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤት ርዕሰ መምህርን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላት÷ አቶ በቀለ በሥራቸው ታዛዥና ታታሪ መሆናቸውን ገልጸው ፍላጎታቸው እንዲሳካ በማበረታታት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡