በትግራይ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት 11 ተጠሪ ተቋማት በትግራይ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴዔታ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) እንዲሁም የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ረዳ በመቐለ ከተማ በአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት አስጀምረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን እንደባህል በመውሰድ ሀገርን መገንባት እንደሚገባ ያነሱት ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር)፥ ለዚህም መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፥ ከዚህ በፊት በተለያዩ ክልሎች ተሳትፎ የነበራቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተጠሪ ተቋማት በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብርም በትግራይ እና ሲዳማ ክልሎች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ከ34 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች በተለያዩ ተግባራት እንደሚሳተፉም አብራርተዋል፡፡
በዚህም ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልገሎቱ ተጠሪ ተቋማቱን በማስተባበር የ20 አቅመ ደካሞችን ቤት ለመገንባት፣ ከ2 ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ለመትከል፣ በፅዱ ኢትዮጵያ መርሐ-ግብር ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት ግንባታ እና ለ1 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ለማበርከት መታቀዱም ተገልጿል፡፡
የትግራይ ጊዚያዊ አስተደደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተጠሪ ተቋማትን አመስግነው፥ እንዲህ ስንረዳዳ የዜጎችን ህይወት መቀየር እንችላለን ብለዋል፡፡
ለወደፊቱም እንደነዚህ ዓይነት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀው፥ በክልሉ በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ በተለያዩ ተግባራት የክረምት በጎ ፈቃድ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በዚህም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብርን ያስጀመሩ ሲሆን ፥ መርሐ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት በትግራይ ደቡባዊ ዞን ውስጥ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ፥ በክልሉ የተራቆቱ ተራሮች መልሰው እንዲያገግሙ ሁሉም ህብረተሰብ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በንቃት ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል።
የተራቆተ ደን ለመመለስና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር ችግኝ መትከልና መንከባከብ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ