የአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከዛሬ ሰኔ 22 ጀምሮ እስከ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ይከናወናሉ።
በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው ውድድር ጥሎ ማለፉን የተቀላቀሉ ብሔራዊ ቡድኖች ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ስዊዘርላንድ ከዩሮ 2020 ሻምፒዮኗ ጣሊያን ጋር ትገናኛለች።
የሁለቱ አሸናፊ ቡድን በሩብ ፍጻሜው ከእንግሊዝና ስሎቫኪያ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
ጣሊያን በምድብ ማጣሪያው ከምድብ ሁለት ስፔንን ተከትላ አራት ነጥብ በመያዝ ከምድቧ ሁለተኛ ሆና ያለፈች ሲሆን፤ በአንጻሩ ስዊዘርላንድ አምስት ነጥብ በመያዝ ከምድቧ በተመሳሳይ ጀርመንን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ነው ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችው።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ደግሞ አስተናጋጇ ጀርመን ከዴንማርክ ጋር ትጫወታለች።
ጀርመን ከምድብ አንድ ሰባት ነጥብ በመያዝ በቀዳሚነት በማጠናቀቅ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች ሲሆን፤ ዴንማርክ ደግሞ ሶስቱንም የምድብ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ከምድብ ሶስት እንግሊዝን በመከተል ሁለተኛ ሆና ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏ ይታወቃል።
የጀርመንና ዴንማርክ አሸናፊ በሩብ ፍጻሜው ከስፔን እና ጆርጂያ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።