Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ምን ውጤቶችን አስመዘገቡ?

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ምክክር የተለያዩ ውጤቶችን አስገኝቶላቸዋል።

ሀገራት የምክክር ሂደት ውስጥ እንዲገቡ ያስፈለገበት ምክንያት የሚለያይ ቢሆንም በብዙ ሀገራት የተደረጉ የምክክር ሂደቶች ተቀራራቢ ውጤቶችን አምጥተዋል።

ከዚህ በመቀጠል የሚብራሩት ሀሳቦች በሂደቱ ካለፉ ሀገራት ልምድ በመነሳት እንደ ውጤት የተመዘገቡ ዋና ዋና ክስተቶች ናቸው፡፡

የፖለቲካ ሥርዓት ማሻሻያ

ምክክሩ የፖለቲካ ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ሲያቀርብ ሀገራት የቀረቡትን ምክረ ሀሳቦች መሰረት አድርጎ አዳዲስ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን፣ አሰላለፎችን ብሎም መዋቅሮችን አስተናግደዋል፡፡ ይህንንም መሰረት በማድረግ መንግስታት የህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚ እና ህግ ተርጓሚ አካላትን መዋቅር በማስተካከል ተቋማዊና መዋቅራዊ ለውጦች እንዲመጡ አድርገዋል፡፡

ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያዎች

ሀገራዊ ምክክሩ ከሚያስገኛቸው ውጤቶች አንዱ ህገ-መንግስትን ማሻሻል ነው፡፡ በሂደቱ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ሀገራቱ ህገ-መንግስቶቻቸውን ሽረው በአዲስ መልክ መቅረፅን ጨምሮ በተመረጡ አንዳንድ አንቀጾች ላይ ማሻሻያዎችን አካሂደዋል፡፡

የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች

በሕዝብ ዘንድ የሚነሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች (ችግሮች) በምክክሩ ሂደት የሚታዩ ናቸው ፡፡ ይህንንም መሰረት ባደረገ መልኩ መንግስታት (ሌሎች ባለድርሻ አካላት) ከመልካም አስተዳደር፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወዘተ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉባቸውን ተግባራዊ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች

የሰብዓዊ መብት የሰው ልጅ መሰረታዊ መብት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በህይወት የመኖር መብት እንዲሁም ሀሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት ጨምሮ የሴቶች እና ሕፃናትን መብቶችን ማስጠበቅ የሀገራዊ ምክክር ተጠቃሽ ውጤቶች ሆነው ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡

ቀደም ሲል ለተፈፀሙ በደሎች መፍትሔ ማበጀት

የሀገራዊ ምክክር ሌላኛው ውጤት በግጭት ውስጥ የቆዩ የተለያዩ ጎራዎች (አካላት) ስላሳለፉት የግጭት እና የቅራኔ ኩነቶች በግልፅ ተነጋግረው ወደ መፍትሔ መሄዳቸው ነው፡፡ የተለያዩ ሀገራት በሂደቱ የተፈጠሩ ጉዳቶችና በደሎች መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገዶች በማመቻቸት፤ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ዘላቂና ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንዲመሰረት አስችለዋል ሲል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.