የድምፅ ኮሮጆዎች ከምርጫ ጣቢያ ወደ ምርጫ ክልል ጽ/ቤት ገብተዋል- የሆሞሻ ምርጫ ክልል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው ዙር ቀሪ ሀገር አቀፍ ምርጫ መጠናቀቁን ተከትሎ የድምፅ ኮሮጆዎች ከምርጫ ጣቢያዎች ወደ ምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት መግባታቸውን የሆሞሻ ምርጫ ክልል ገለፀ።
የሆሞሻ ምርጫ ክልል ኃላፊ አዲሱ ገዳፌ እንዳሉት÷ በምርጫ ክልሉ ውስጥ የድምፅ አሰጣጡና ቆጠራው በስኬት ተጠናቅቋል፡፡
በምርጫ ክልሉ ከሚገኙ 24 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ይወክለኛል ያሉትን ፓርቲ በነፃነት ድምፅ መስጠታቸውንም ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡
ከምርጫ ጣቢያዎች ወደ ማዕከሉ የገቡ የድምፅ ኮሮጆዎችን ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጓጓዝ ሥራው እንዳሚቀጥልም ነው ያመላከቱት፡፡
ከተመዘገቡት 8 ሺህ 300 አካባቢ እስከ አሁን ባለው የድምፅ አሳጣጥ ሂዳት 5 ሺህ 214 መራጮች ድምፅ ሰጥተዋል ብለዋል፡፡
በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የሁሉም ፓርቲዎች ወኪሎች በተገኙበት ፍታሐዊ ምርጫ መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡