በደሴ ከተማ ጽዱ አካባቢና ጽዱ ጤና ተቋማት ለመፍጠር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ጽዱ አካባቢና ጽዱ ጤና ተቋማት ለተሟላ ጤንነት” በሚል መሪ ሀሳብ የደሴ ከተማ ጤና መምሪያ ጽዱ አካባቢና ጽዱ ጤና ተቋማት ለመፍጠር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የከተማው ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ የሱፍ÷የጽዳት ንቅናቄው የግል ንፅህናን ከመጠበቅ ጀምሮ የህክምና መስጫ ክፍሎችንና አካባቢን ሁልጊዜም ጹዱ ማድረግን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መርሃ ግብሩ በቀጣይ በሁሉም የጤና ተቋማት ላይ ተደራሽ እንደሚሆንና ወጥ የሆነ የስራ መርሃ ግብር ወጥቶለት የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ በየደረጃው የግንዛቤ ፈጠራ ስራም እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው በበኩላቸው÷ ንቅናቄው ፅዱና ጤናማ አካባቢን ከመፍጠር አንፃር ያለው ሚና ከፍተኛና ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡