Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚከናወነው ሥራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲል የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጠየቀ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ከብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ መንግስትና ህዝቡ የሚፈልጉትን ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል፡፡

የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን 371 ሺህ 971 የሚደርሱ የቀድሞ ታጣቂዎች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሴቶችን ይዞ ወደ ሥራ ለመግባት ፕሮጀክት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንዳሉት÷ ይህን ያህል ቁጥር ያለውን የሰው ሃይል ትጥቅ አስፈትቶ፣ በቂ የሥነ-ልቦና ስልጠና ሰጥቶ፣ የመልሶ ግንባታና መልሶ የመቀላቀል ሥራ መስራት የአምራች ሃይሉን ቁጥር ከፍ ያደርጋል፡፡

ለሀገር ውስጥ ሰላም መስፈን የራሱን ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሥራውን በስኬት ለማከናወንም ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና አስተዋፅኦ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ መከላከያ ሚኒስቴር በትኩረት ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል የመልሶ ማቋቋም አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የረጅም ጊዜ ልምዳችን እና በዘርፉ ላይ የተሰማራውን የሰው ሃይል በመጠቀም ለሀገር የሚበጅ የሰላም እና የልማት ሃይል እንዲፈጠር በቅንጅት እንሰራለን ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.