Fana: At a Speed of Life!

በባሕር ዳር የኮሪደር ልማት ሥራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የኮሪደር ልማት መርሐ-ግብር በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

ከተሞችን ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሀገራዊ መርሐ-ግብር አካል የሆነው የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት የዲዛይን ጥናት ሥራ ተጠናቅቆ ርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በተገኙበት ተጀምሯል፡፡

አቶ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ልማቱ የክልሉ ከተሞች ራሳቸውን የሚያድሱበት፣ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትና ለነዋሪዎች ምቹ በመሆን የታሪክና የባህል ማዕከልነታቸውን ዘመኑን በሚመጥን መንገድ የሚያስቀጥሉበት ነው፡፡

ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ከተሞችን መፍጠር የምንችለው ለእንግዶችም ሆነ ለነዋሪዎች የተመቹ ዘመናዊ ከተሞችን መገንባት ስንችል በመሆኑ የኮሪደር ልማቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት መርሐ-ግብሩን በባሕር ዳር ከተማ ውጤታማ አድርጎ ለመምራትም በየደረጃው ያለውን አመራር ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ውጤታማነት ለሌሎች የክልሉ ከተሞች የሚተርፍ መሆኑንን መገንዘብ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በባሕር ዳር ከተማ ለሚጀመረው የኮሪደር ልማት ልምድ በማጋራት እና ለዲዛይን ዝግጅቱ ውጤታማነት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በክልሉ ሁሉም ሪጂዮ ፖሊታን ከተሞች የሚከናወን የኮሪደር ልማት የማስጀመሪያ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የሚሠሩ ሕንጻዎችን ከፍታ፣ ቀለማቸው፣ በመንገድ ዳር የሚከናወኑ ልማቶችን የሚወስን እንዲሁም የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች፣ የታክሲና አውቶቡስ ማቆሚያዎች፣ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች፣ ማረፊያዎች፣ ካፌዎችንና ሌሎችን እንደሚያካትትም አብራርተዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት 22 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንም አስታውቀዋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.