Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2016 በጀት ዓመት 11 ወራት 23 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ፤ ተቋሙ በሀገሪቱ ባሉት 25 ቅርንጫፎች ከ200 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት መቀበሉን ተናግረዋል።

በዚህም 23 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን መገበያየቱን ገልጸዋል።

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቡና 18 በመቶ እንዲሁም የቅባት እህሎች 45 በመቶ ብልጫ እንዳላቸው ገልጸው፤ ሌሎች ምርቶችም በተመሳሳይ እድገት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ እድገት አለው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ምርት ገበያው አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለውጭ ገበያ የሚውሉ ባቄላ፣ ኑግና ሽንብራ በቅርቡ ወደ ግብይት ሥርዓቱ ያስገባቸው አዳዲስ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን ምርቶች ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በምርት ገበያው እንዲሁም በውልና ኢንቨስትመንት እርሻ በኩል ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።

የቢራ ገብስ፣ ዳጉሳ፣ ተልባ፣ ቆዳና ሌጦ እንዲሁም የጥጥ ምርቶች ላይ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የቢራ ገብስን መቀበል የሚያስችል ጥናት ተጠናቆ የግብይት ውል መጽደቁን ተናግረዋል።

በመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት 30 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ምርቶችን በመጋዘን በማከማቸት ከባንኮች ጋር ብድር የማመቻቸት ሥራ የተከናወነ ሲሆን ወደ 4 ሚሊየን ብር ብድር መለቀቁን ጠቁመዋል።

የመጋዘን አገልግሎትን ለማስፋት የላብራቶሪ አቅምን በማደራጀት ከአንድ ምርት በላይ እንዲቀበሉ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

ምርት ገበያው በሰው ኃይል አቅም ግንባታና በምርምር ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ለአፍሪካም የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.