Fana: At a Speed of Life!

በካሊፎርኒያ 50 ኪሎ ሜትር ካሬ የሸፈነ ሰደድ እሳት ተቀስቅሶ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ከሎስ አንጀለስ ሰሜን ምዕራብ የተቀሰቀሰ ሰደድ እሳት 50 ካሬ ኪሎ ሜትር ካሬ ቦታ እንደሸፈነና ነዋሪዎች እንዲለቁ ማስገደዱ ተገለጸ።
 
ሰደድ እሳቱ ከአንድ ሺህ በላይ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲለቁ ማስገደዱን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
 
የካሊፎርኒያ የደን እና የእሳት አደጋ መከላከል ክፍል (ካል ፋየር) እንደገለጸው÷ 400 የሚሆኑ የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ 70 የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች እና ሁለት መንገድ ጠራጊ ማሽኖች እሳቱን ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
ሰደድ እሳቱ ከሎስ አንጀለስ በስተሰሜን ምዕራብ በ96 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በካሊፎርኒያ በጎርማን በስተደቡብ እየተቀጣጠለ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
 
ቅዳሜ ከሰአት በኋላ የጀመረው ሰደድ እሳት ወደ ደቡብ ምስራቅ ፒራሚድ ሀይቅ እያቀና እንደሚገኝም ”ካል ፋየር” አስታውቋል።
 
ሰደድ እሳቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ 1 ሺህ 200 የሚሆኑ ሰዎች ሃንጋሪ ከተሰኘው የመዝናኛ ስፍራ ለቀው ለመሄድ መገደዳቸውም ተነግሯል፡፡
 
እስካሁን በእሳቱ የመጎዳት አደጋ ላይ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ባይኖሩም÷ ሁለት የንግድ ህንፃዎች ላይ ግን ጉዳት መድረሱን የሎስ አንጀለስ ግዛት የእሳት አደጋ መከላከል ክፍል አስታውቋል።
 
ካል ፋየር እንዳስታወቀው÷ ሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በከፍተኛ ሙቀት፣ ዝቅተኛ እርጥበት እና ኃይለኛ ንፋስ ምክንያት እየተስተጓጎለ መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
 
ይሁን እንጂ ውሃ የሚረጩ አውሮፕላኖች እሳቱ እንዳይስፋፋ ለመከላከል እየሰሩ እንደሚገኝና የእሳት አደጋ ሠራተኞችም እሳቱን የበለጠ ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የእሳት አደጋ መከላከያ መስመሮችን በመገንባት ላይ መሆናቸው ተመላክቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.