የአረፋ በዓል ተግባራት
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ የመስዋዕት በዓል ተብሎ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ተከብሮ ይውላል፡፡
ሐይማኖታዊ ምክንያቱም ነብዩ ኢብራሂም ፈጣሪያቸውን የመስማትና ለዚያም እስከልጅ መስዋዕት ማድረግ የደረሰን ፍቅር እንደሚያሳይ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡
ነብዩ ኢብራሂም በህልማቸው አላህ ልጃቸው እስማኤልን እንዲሰው ሲጠይቃቸው በማየታቸው ፈቃዱን ለመሙላት አላንገራገሩም ይላሉ የኃይማኖቱ አባቶች፡፡
በዚህም ነብዩ እስማኤል ይህን በመገንዘብ አባታቸው ራርተው የአላህን ፈቃድ እንዳይሽሩና ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ይነግሯቸዋል ፤ በዚህም ለመስዋዕት ይዘጋጃሉ፡፡
ሆኖም አላህ የኢብራሂምን ልጅ እስከመሰዋት የደረሰ ፍቅርን እና መታመንን እንዲሁም የእስማኤልን ታዛዥነት በማየት በምትኩ በግን ለመስዋዕት ያበረክታል፡፡
ይህን ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ተከትሎ ህዝበ ሙስሊሙ አቅሙ የፈቀደውን እርድ (ኡዱሁያ) በመከወን ያለው ለሌለው በማካፈል የአላህን ፍቃድ ይፈጽማል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም አቅማቸው የፈቀደላቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች የሐጅ ሥነ-ሥርዓትን በማድረግ ስለዓለም ሰላም፣ ስለቤተሰብ፣ ከሃጥያት ስለመከልከልና በዚያም ጽድቅን ስለመሻትና ጀነትን ስለመውረስ ዱኣ ያደርጋሉ፡፡
አቅማቸው ያልፈቀደላቸው የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ እስላማዊ ሥነ-ሥርዓትንና ሕግጋቱን ጠብቀው ያላቸውን በማካፈል፣ በዱኣ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶችን በማከናወን ያከብራሉ፡፡
የአካበበር ሥነ-ሥርዓቱ እንደየሀገሩ ቢለያይም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ሙስሊሞች በልባቸው ያለውን የአላህ ቃል የሚፈጽሙበትና የሚባረኩበት ዕለት ነው፡፡
ኩርባኒ ወይም መስዋዕት በዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ትልቁ ተግባር ሲሆን፥ሙስሊሙ እንደየአቅሙና እንደፍላጎቱ የበግ፣ ላም፣ ፍየል፣ ወይም ግመል እርድን ይፈጽማል ፤ እርዱም ከሦስት ይከፈላል፡፡
ይህም ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ለአቅመ ደካሞችና ለሚያስፈልጋቸው በማጋራት የፈጣሪን ተካፍሎ የመብላት አስተምህሮ በተግባር የሚገልጡበት ነው፡፡
ምክንያቱም ቀኑ ከራስ ፍላጎት በላይ የአላህን ፍቃድና አስተምህሮ እንዲሁም ፍቅርን በተግባር የሚገልጡበት የመስዋዕት በዓል ስለሆነ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ህዝበ ሙስሊሙ ልዩ የዱኣ ሥነ-ሥርዓትን የሚካፈል ሲሆን ፥ በዚህም በመስጅድ በመሰባሰብ ለፈጣሪ ምስጋናና ጸሎታቸውን ያደርሳሉ፡፡
በበዓሉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከዘመድ አዝማድ የሚገናኝበትና ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት በዓል ሲሆን ፥ በሌሎች ዘንድም ሀሴትን የሚሞሉበት የመስጠትና የማጋራት ቀን ነው፡፡
በመሰረት አወቀ