Fana: At a Speed of Life!

ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ኤርትራክተሮችን ወደ ስራ አስገብተናል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እጅግ ዘመናዊ የሆኑ፣ ለግብርናው ዘርፍ አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ኤርትራክተሮችን ዛሬ ወደ ስራ አስገብተናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ግብርናችን የህልውናችን እና የሉዓላዊነታችን መሰረት ነው ብለዋል።

ዘርፉን ከሚገጥሙት ፈተናዎች ለመታደግ ዘመኑ የደረሰባቸውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን መታጠቅና መጠቀም የግድ እንደሆነም ገልጸዋል።

በዓለም የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ለተባይ ርጭት፣ ለእሳት ማጥፊያና ለሌሎችም አገልግሎቶች ምቹና እጅግ ዘመናዊ የሆኑ፣ ለግብርናው ዘርፍ አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ኤርትራክተሮችን ዛሬ ወደ ስራ አስገብተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ዘመናዊ ኤርትራክተሮችን ከተባይ እና አንበጣ አሰሳና መከላከል ባሻገር የእሳት አደጋን በመቆጣጠር፣ የአፈር እርጥበት መረጃን በማሰባሰብ ረገድ ያላቸው ሚና ላቅ ያለ በመሆኑ ለጀመርናቸው ስራዎች የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ኤርትራክተሮቹ የተፈጥሮ እና ድንገተኛ አደጋ በሚፈጠርበት ጊዜ ከሀገራችን አልፈው በቀጠናው እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ኤርትራክተሮቹ ለግሉ ሴክተር እና ለትላልቅ የንግድ እርሻዎች አገልግሎት በመስጠት የውጪ ምንዛሬ በማስገኘቱ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.