Fana: At a Speed of Life!

በ2017 የትውልድ ምርታማነትን ማስቀጠል ይገባል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የሰላም ሁኔታዎቻችንን ማፅናት እንዲሁም የትውልድ ምርታማነትን ማስቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ የ2016 በጀት ዓመት አስር ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች ዋና ዋና አፈፃፀም ዛሬ መገምገሙን ገልጸዋል።

በግምገማው በአስፈጻሚ አካላቱ በዕቅድ የተያዙ ስራዎችና የሪፎርም አተገባበሮች ውጤታማ እንደሆኑ ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡

በበጀት አመቱ ያቀድነውን ልማት እውን ለማድረግ የሀገርን ፀጋና ሃብትን ከመለየት ባሻገር ያስመዘገብናቸውን ድሎች ቀጣይነት ማስቀጠል እንደሚገባ ተነጋግረናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁለት ምክንያት መበልፀግ እንዳለባት አንስተው፤ አንደኛው አቅም ስላላት፣ ማድረግ ስለምትችል እና ሰርታ በማሳየቷ ሲሆን÷ ሁለተኛው ደግሞ የሀብት ችግር ስለሌለባትና የበቂ ሀብት ባለቤት በመሆኗ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በቀሪ ወራት መፈፀም ያለባቸው ተግባራትን በመለየት በዓመቱ ለማሳካት የተያዙ ትልሞችን በተሟላ መልኩ ለመፈፀም ከስራ ኃላፊዎች ጋር የጋራ መግባባት መፈጠሩንም አመላክተዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በሰላም እና ፀጥታ፣ የፕሮጀክት አፈፃፀም ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባም ገምግመናል ነው ያሉት።

በ2017 የትኩረት አቅጣጫዎች ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ የተጀመሩ የሪፎርም ንቅናቄዎችን መሬት ማስነካት እና አካታች ማድረግ፣ የሰላም ሁኔታዎችን ማፅናት እንዲሁም የትውልድ ምርታማነትን ማስቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.