Fana: At a Speed of Life!

ከአረብ ሀገራት የሚመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአረብ ሀገራት የሚመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ በ100 ቀናት የግምገማ መድረክ በማህበራዊ ጉዳዮች የተነሱ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ባለፉት 10 ወራት በህገ ወጥ መንገድ የተሰደዱ ዜጎችን የመመለስና የህፃናትን ጥቃት መከላከል የሚያስችሉ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጉዲፈቻ ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ስርዓት ከማጠናከር አኳያም 200 የሚሆኑ ልጆች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ ልጆች የሀገራቸውን ማንነት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምትከተለው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በውጭ ሀገራት ታስረው የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከሳዑዲ አረቢያ፣ ኦማን እና ሱዳን 90 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ የተቻለ ሲሆን÷ ተመላሾችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የወጣቶችን ህገ ወጥ ስደት በመግታት በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ በተግባር ለማሳየት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ተቀርፆ ስራ ላይ መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡

የህፃናትን ጥቃት በመከላከል ረገድም ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የህፃናት መረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋቱንም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የህፃናት መረጃ አያያዝ ሥርዓቱ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎችም ይተረጎማል ብለዋል።

በቀበሌዎች የማህበረሰብ ጥምረት በማቋቋም የህፃናትን የጥቃት ተጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በዚህ የተቀናጀ አሰራርም 1 ሺህ 40 ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህፃናትን ወደ ጎዳና ከመውጣት ታድገናል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.