2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት አራት ተቋማት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።
ሥምምነቱን የፈረሙት ተቋማትም÷ ጤና ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና የሩስያ ፓን- አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ናቸው፡፡
በሥምምነቱ መሠረት ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይና 2 ሺህ የጤና ማዕከላት ለመገንባት እንደሚሰራ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ደረጄ ዱጉማ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ማዕከላቱ በዋናነት በእናቶችና ሕጻናት ጤና፣ በአረጋውያን፣ በወጣቶች እንዲሁም በወሊድ፣ በክትባት፣ በቤተሰበ እቅድና በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እያንዳንዳቸው ማዕከላትም ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚጠጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላሉ ብለዋል።
ለአጠቃላይ ግንባታውም ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚፈጅና ወጪውም በሩስያ ፓን- አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት እንደሚሸፈን አስታውቀዋል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ዓለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው÷ ሥምምነቱ የእናቶችን ብሎም የሕጻናትን ጤና ለመጠበቅ አቅም እንደሚፈጥር አስገንዝበው÷ ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የሚጠበቅበትን ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
የሩስያ የፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት ግብረ-ሰናይ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦክሳና ማዮሮቫ÷ ፕሮጀክቱ የዜጎችን ጤናማ ሕይወት ለማስጠበቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይህን ፕሮጀክት ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ እውን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ናቸው።