ግለሰብን ደብድበው ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘የሆቴል ደንበኛን ረብሸሃል’ በሚል ሰበብ ግለሰብን በመደብደብ ሕይወቱ እንዲያልፍ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ ተከሳሾች በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ጅማ ዞን ዐቃቤ ሕግ ዮናስ አጥናፍ እና አማኑኤል ጥላሁን የተባሉ ተከሳሾች ላይ ባቀረበው የግድያ ወንጀል ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው÷ ተከሳሾቹ በጅማ ከተማ በሚገኘው ደጊቱ ሆቴል ውስጥ በ “ጋርድነት” ሲሰሩ ካልተያዘ አንድ ግብረ አበር ጋር በጋራ ሆነው ከድር ሙሳ የተባለ የግል ተበዳይን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም በሆቴሉ ውስጥ ሲዝናና “ከዚህ በፊት ረብሸሃል ውጣ” በማለት በተፈጸመበት ድብደባ በደረሰበት ጉዳት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ የጅማ ከተማ ፖሊስ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ካስረከበ በኋላ በተከሳሾቹ ላይ ክስ ተመስርቷል፡፡
ተከሳሾቹ ክሱ በችሎት ከደረሳቸው በኋላ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው÷ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም÷ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ተከሳሾቹ ያቀረቡትን ሦስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየትና የዐቃቤ ሕግ ቅጣት ማክበጃ አስተያየትን በመያዝ ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸውን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ወስኗል፡፡
በታሪክ አዱኛ