Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ ናት – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሰላምን እና እድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለፁ፡፡

በሩሲያ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት አምባሳደር ታዬ፤ ኢትዮጵያ ለብሪክስ አባልነቷ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ በመድረኩ ላይ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ ያላትን የጎላ ሚና ለማሳደግም ከብሔራዊ የልማት ትኩረቶቿ አኳያ የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችን አብራርተዋል።

ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የሆኑ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ጥቅም ለማስጠበቅ የባለብዙ ወገን ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ የልማት ፋይናንስ እና የዕዳ ስረዛ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሰላምን እና እድገትን፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ልማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕከል ያደረጉ እና የጋራ መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ ውጤታማ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች በስበሰባው አፅንኦት እንደተሰጣቸውም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል::

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.