የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባህር ዳርና ጎንደር ገቡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ተስፋየ ይገዙ ባሕር ዳር ከተማ ገብተዋል።
መሪዎቹ ባሕር ዳር ሲደርሱ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
መሪዎቹ በባሕር ዳር ከተማ በሚኖራቸው ቆይታ በከተማዋ ውስጥ በመገንባት ላይ ያሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ተዘዋውረው ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አሚኮ ዘግቧል።
በባሕር ዳር ከተማ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በሚደረገው የውይይት መድረክ ላይም እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ እርስቱ ይርዳው የስራ ጉብኝት ለማድረግ ጎንደር ከተማ ገብተዋል።
ልዑካኑ ጎንደር ከተማ ሲገቡ የአማራ ክልል አመራሮች፣ የከተማው ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሀይና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በቆይታቸው በከተማው ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችን ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን÷ ውይይቶችንም ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።