Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የውሃ ችግርና የአየር ንብረት ቀውስ ለመቋቋም ጥረት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የዓለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የውሃ ችግርና የአየር ንብረት ቀውስ ለመቋቋም ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአየር ንብረት ቀውሱ በአፍሪካ ቀንድ የውሃ ችግርን እያባባሰ በመምጣቱ የተመድ ኤጀንሲዎች፣ የዓለም ባንክ እና የቀጣናው ድርጅቶች በውሃ አስተዳደር ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ስምንት የተመድ ኤጀንሲዎች፣ የዓለም ባንክ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን፣ የልማት እና የሰብአዊ አጋሮች፣ የሲቪክ ማህበራት እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በኬንያ ናይሮቢ ተገኝተው ቀጣናዊ የውሃ ላይ ትብብርን ለማጠናከር መክረዋል።

እንደ ድርጅቶቹ ገለጻ፥ በአፍሪካ ቀንድ በተደጋጋሚ በድርቅና ጎርፍ የተጠቁ አካባቢዎች ከአምስት ሰዎች አንዱ ንፁህ ውሃ አያገኝም፡፡

በናይሮቢ አጋሮቹ በሰጡት መግለጫም፥ በቀጣናው የሚኖሩ ህዝቦች ዛሬም ቢሆን ወደፊት እንዲበለፅጉ የልማትና የአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲሁም በትብብር እና በፈጠራ ተነሳሽነት ኢንቨስትመንቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡

30 በመቶው የሚሆነው የቀጣናው ህዝብ በደረቃማና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች የሚኖር በመሆኑ ለውሃ እጦት ስጋት እንደሚጋለጥም ነው የጠቆሙት፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም፥ አብዛኛው የቀጣናው ህዝብ ቢያንስ ለሦስት ወራት ያህል የውሃ እጥረት እንደሚገጥመው ገልጸዋል።

በዚህም ድርጅቶቹ የተቀናጀ እርምጃ ካልወሰዱ የውኃ እጥረትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ቀውሶች በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ አሉታዊ ጫና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸውን የዘገበው ዥንዋ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.