Fana: At a Speed of Life!

የሲንጋፖር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲንጋፖር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም በኢትዮጵያ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሲንጋፖር ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሲንጋፖር አቻቸው ቪቪያን ብላከሪሽናን (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው እንዲሁም የጋራ ትብብርን በሚጠይቁ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች በተለይ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የልማት ትብብሮች ዙሪያ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሲንጋፖር በአለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን ያላትን ስትራቴጂካዊ ስፍራ አድንቀዋል።

በዚህም የሲንጋፖር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስማርት ከተማ ልማትና ስማርት ግብርናን በማስፋት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም አገልግሎትና በትምህርት ዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቪያን ብላክሪሽናን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሲንጋፖር በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ተሳትፎዋን ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢን ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ፊት ያለውን መልካም እድል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.