Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸውን የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ተቀዳሚ ምክትል ሚኒስትር ኪም ባይንግ-ህዋን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት አህመድ ሺዴ ሀገራቱ በደም መስዋዕትነት ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው፤ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር የአንድ ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ስምምነት በመፈራረሟ ምስጋና አቅርበዋል።

ኮሪያ ሪፐብሊክ የገንዘብ ድጋፏን እንድታሳድግ የጠየቁት ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ 126 ሚሊየን ህዝብ ያላት፣ ፈጣን ኢኮኖሚ መስፋፋት እያሳየች ያለች እና በፋይናንስ ማሻሻያ ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።

የሀገራቱን የገንዘብ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም አቶ አህመድ ሺዴ ቃል ገብተዋል።

የኮሪያ ሪፐብሊክ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ተቀዳሚ ምክትል ሚኒስትር ኪም ባይንግ-ህዋን በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።

ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት መጠቆማቸውንም በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

ከዚህም በተጨማሪ ኪም ባያንግ-ሁዋን ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ዘርፎች እውቀትና ልምድ ለመለዋወጥ ቃል ገብተዋል።

ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከሁለቱ ሀገራት አጋርነት በተጨማሪ የባለብዙ ወገን ትብብር ያለውን ፋይዳም አፅንዖት ሰጥተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.