Fana: At a Speed of Life!

በዩክሬን የሰላም ጉባዔ ላይ ሀገራት እንዳይሳተፉ እንቅፋት አልሆንኩም- ቻይና

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በዚህ ወር በስዊዘርላንድ መሪነት በሚካሄደው የዩክሬን የሰላም ጉባዔ ላይ “ሌሎች ሀገራት እንዳይሳተፉ ለማስቆም ሙከራ አለማድረጓን” አስታወቀች፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ከጉባዔው ጎን ለጎን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ÷ “ቻይና ጉባዔውን ለማደናቀፍ እየሠራች ነው” ሲሉ ኮንነዋል፡፡

ቻይና ለሩሲያ የምታደርገው ድጋፍም ጦርነቱን እንደሚያራዝመው ጠቁመው ይህም በዓለም ላይ አሉታዊ ውጤቶችን ያመጣል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

ሩሲያም ብትሆን የቻይና ዲፕሎማቶችንና በቀጣናው ያላትን ሚና ተጠቅማ የሰላም ጉባዔውን ለማደናቀፍ ልትጥር እንደምትችል አመላክተዋል፡፡

የቻይና ድርጊት የራሷን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን የማስከበር ጥያቄን የሚቃረን ስለመሆኑም በማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማዎ ኒንግ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ “የቻይና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የበላይነትን ወይም ማስገደድን አያካትትም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ቻይና ግልፅ እና ገለልተኛ እንዲሁም በሌሎች ላይ ጫና በመፍጠር ውስጥም አትሳተፍም ማለታቸውን ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል።

የቤጂንግ አቋም “ፍትሐዊ እና ገለልተኛ” መሆኑን ገልጸው÷ በጉባዔው ላይም ቻይና ሀገራት እንዳይሳተፉ እንቅፋት አለመሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.