ሐማስ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ሃሳብ በበጎ እንደሚመለከተው አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐማስ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ በአዎንታ እንደሚመለከተው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በነጩ ቤተመንግስት ባደረጉት ንግግር ፥ እስራኤል ስላቀረበቻቸው የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳቦች ገለጻ አድርገዋል፡፡
በገለጻቸውም÷ በመጀመሪያው እቅድ ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም ማድረግ፣ የእስራኤል ወታደሮች ህዝብ ከሚበዛባቸው አካባቢዎች ለቆ መውጣት እና እስረኞችን መለዋወጥ የሚሉ ሃሳቦች መካተታቸውን አንስተዋል፡፡
በጋዛ ያለውን ግጭት ለማስቆም እስራኤል ያቀረበችውን ሃሳብ ሐማስ እንዲቀበል ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ ፥ በዚህም ጦርነቱ እንዲያበቃ ማድረግ አንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
ፕሬዚዳን ባይደን የጋዛ ጦርነት የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ለ6 ሳምንታት በሚቆየው የተኩስ አቁም የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ህዝብ ከሚበዛባቸው የጋዛ አካባቢዎች የሚወጣ ሲሆን÷ ይህም ለጋዛ የሚደርሰው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲጨምር ያስችላል ተብሏል፡፡
የእስረኞች ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል የተባለለት የተኩስ አቁም ሃሳቡ÷ ሀገራቱ ወደ ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደርሱ እና ለጋዛ የመልሶ ግንባታ ሒደት ሚናው የጎላ እንደሚሆንም ተመላክቷል፡፡
ሃማስ በበኩሉ÷ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ሃሳብ በበጎ እንደሚመለከተው አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ÷በጋዛ ብዙ ስቃይ እና ውድመት ተመልክተናል ፤ይህ የሚቆምበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው ሁለቱም ወገኖች የተኩስ ማቆም እድሉን እንዲጠቀሙ የመከሩ ሲሆን ፥ እስረኞች እንዲፈቱና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ፤ በዚህም በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ሰላም እንደሚሰፍን ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጋዛ ከ36 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን በሐማስ የሚመራውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡