ዩክሬን ከአውሮፓ ተጨማሪ ድጋፍ አገኘች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ፑቲን ሩሲያን መንካት እንደማይቻል እያስጠነቀቁ ባሉበት ወቅት ዩክሬን ከአውሮፓ ተጨማሪ ድጋፍ ማግኘቷ ተገልጿል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በአውሮፓ ሀገራት ያደረጉት ጉብኝትን በፖርቹጋል ለማጠናቀቅ ፖርቹጋል ገብተዋል።
በዚህም ከፖርቹጋል ጋር በጸጥታ ጉዳይ በጋራ ለመስራት የ10 ዓመት የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
በፖርቱጋል እና በዩክሬን መካከል በተፈረመው ስምምነት መሠረትም÷ ፖርቹጋል በዚህ ዓመት ለዩክሬን መልሶ ግንባታ የሚውል 126 ሚሊየን ዩሮ ትሰጣለች።
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ፖርቹጋል ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፖርቹጋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሉዊስ ሞንቴኔግሮ ተናግረዋል፡፡
የቼክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔትር ፊያላ በበኩላቸው፤ ለዩክሬን ተተኳሽ ለመግዛት 15 የአውሮፓ ህብረት ሀገራት እና ኔቶ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዩሮ በላይ አበርክተዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የመጀመሪያዎቹ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ባለ 155 ሚሊ ሜትር የመድፍ ተተኳሾች በሰኔ ወር ወደ ዩክሬን እንደሚደርሱና የመጀመሪያው የመርከብ ጭነትም በሚቀጥሉት ቀናት ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
ምዕራባውያን ሀገራት ወታደራዊ ተሳትፎአቸውን ቢያጠናክሩም፤ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ እንደምትቀጥል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ትናንት ማስታወቃቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።