አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በፓሪሱ ኦሎምፒክ የስፖርት ቤተሰቡ የተለመደውን ድጋፍ እንዲሰጠው ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ የመጨረሻ ድሉን ለማስመዘገብ በሚያደረገው ጥረት የስፖርት ቤተሰቡ የተለመደውን ድጋፍ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡
አትሌቱ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በመወከል እንዲሳተፍ ያደረገው ጥረት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገፁ የምስጋና መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም “በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሀገሬን ለመወከል እድል በማግኘቴ ደስ ብሎኛል፤ በአትሌቲክስ ሕይወቴም የመጨረሻ ድሌን ለማስመዝገብ ተዘጋጅቻለሁ” ብሏል፡፡
በስኬታማ የአትሌቲክስ ጉዞው የስፖርት ቤተሰቡ ድጋፍና እምነት የጥንካሬው ምንጭ መሆኑ ገልጾ÷ ስንደጋገፍ እና አንድ ስንሆን ትልቅ ነገር ስለምናሳካ በፓሪስ ኦሊምፒክም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥል ብሏል፡፡
የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ከፈረንጆቹ ሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11 ቀን 2024 ድረስ በፓሪስ እንደሚካሄድ የወጣው መርሐ-ግብር አመላክቷል፡፡