Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ጎበኙ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ላይ ያላቸው ድርሻ እንዲሻሻል በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የሀገር ውስጥ ምርትና አምራቾችን ማጠናከር፣ መሪ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ መገንባት፣ ጥናትና ምርምርን ማሳደግ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስ ከባቢን መፍጠር ደግሞ ከንቅናቄው የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።

በንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ 56 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ነው የተባለው።

መንግስት 96 የሚሆኑ ምርቶችን በመለየት በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራ እንደሚገኝም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

ስትራቴጂው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስ እና የቢራ ብቅልን ጨምሮ አንዳንድ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ ተጠቅሷል።

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.