የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአንዳንድ ኤምባሲዎች የደቦ መግለጫዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አንዳንድ ኤምባሲዎች በደቦ የሚያወጧቸውን መግለጫዎች ኢትዮጵያ እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ የሀገሪቱን አበይት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ ኤምባሲዎች የሚያወጧቸው የጋራ መግለጫዎች ከተለመደው የዲፕሎማሲ አሰራር ያፈነገጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የዓለም የፕሬስ ቀንን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ኤምባሲዎች በጋራ የሰጡት መግለጫ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የደቦ መግለጫዎችን እንደማትቀበል ቃል አቀባዩ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ጽኑ አቋም እንዳለው ገልጸው፤ ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የነባር እና አዳዲስ የዲጂታል ሚዲያዎች ቁጥር መስፋፋት የፕሬስ ነጻነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።
የፕሬስ ነጻነት መብት ሊከበር የሚገባው በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ውስጥ እንደሆነም አስገንዝበዋል።