በግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም 2 የስራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም 2 የስራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል፡፡
ፕሮግራሙ በግሎባል ክላይሜት ፈንድ (ጂሲኤፍ)የፋይናንስ ድጋፍ በ165 ሚሊየን ዶላር በጄት በአለም ባንክ አመቻችነት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአምስት ዓመት በጀት 165 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥም 107 ሚሊየን ዶላሩ የረጅም ጊዜ ብድር ሆኖ 58 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ የልማት ድጋፍ ነው ተብሏል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ በአየር ንብረት ለውጥ ምክኒያት የሚከሰቱ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የሚቻለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሲገነባ ነው፡፡
በአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ትኩረት ከተሰጠባቸው መስኮች አንዱ መሬትን፣ ደንና የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት መጠቀም እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የግብርና ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ በዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ብሎም የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፕሮግራሙም በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በ9 ክልሎችና በ47 ወረዳዎች ላይ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራሞችን በመተግበር ተጨማሪ 706 ሺህ133 ማህበረሰብን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በዛሬው እለት ይፋ የተደረገውፕሮጀክት በመንግስት፣ በዓለም ባንክ፣ በጂሲኤፍ እና በሌሎች የልማት አጋር አካላት ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡