የደሴ ከተማ የልማት ሥራዎች በችግር ውስጥ ሆኖ አመርቂ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ያሳያሉ – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደሴ ከተማ የልማት ሥራዎች በችግር ውስጥ ሆኖ አመርቂ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ያሳያሉ ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማእከል ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን የተመራ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ቡድን በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።
በከተማዋ በመንግሥትና በሕዝብ ተሳትፎ የተሠሩ የኮሪደር ልማቶች በፌደራል እና በክልል ከፍተኛ የመንግሥት ኀላፊዎች መጎብኘታቸውን የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገልጸዋል።
የከተማዋን ሁለንተናዊ ገጽታ የሚቀይሩ የአስፋልት መንገዶች፣ የመናኽሪያ ግንባታ እና የከተማ ማስዋብ ሥራዎች የጉብኝቱ አካል ነበሩ ብለዋል።
የሥራ ኀላፊዎቹ በተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች ተደስተዋል ያሉት ከንቲባው የከተማ አስተዳደሩን እና ሕዝቡን ማመስገናቸውንም ተናግረዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊ አደም ፋራህ፤ “በደሴ ከተማ የተሰሩ የልማት ሥራዎች በችግር ውስጥም ኾኖ አመርቂ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ናቸው” ብለዋል።
ደሴ ከተማ ሰላሟን ጠብቃ በልማት ሥራዎቿ ተምሳሌት መኾን ችላለች በማለት ገልጸዋል።
የአማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንም ማመልከታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው የደሴ ከተማ የመሠረተ ልማት ሥራዎች አበረታች ውጤት እንደተመዘገበባቸው ገልጸው፤ የልማት ሥራዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አስፈላጊውን ሁሉ ይደረጋል ብለዋል።