በአማራ ክልል የኮሌራ በሽታን ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ የኮሌራ በሽታ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባቲ ወረዳ በሦስት ቀበሌዎች መከሰቱን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ገልጸዋል።
የመከላከል እና የማከም ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ÷ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስም 162 ታማሚዎች የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ጤና ተቋማት እንዲሁም የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች በመተባበር በሽታው እንዳይስፋፋ እየሠሩ መሆኑም ተገልጿል።
ዋና ዳይሬክተሩ ”በሽታው በሌሎች ዞኖች እንዳይከሰት እና ጉዳት እንዳያደርስ ኢንስቲትዩቱ ጥብቅ ክትትል፣ የመረጃ ልውውጥ፣ ትንተና እና ሃብት የማዘጋጀት ሥራዎች እየሠራ ነውመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የሚታይባቸው ሰዎች ሲገኙ በፍጥነት በአቅራቢያ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል መባሉን አሚኮ ዘግቧል።
የቧንቧ ውኃ መጠቀም፣ የወንዝ እና ኩሬ ውኃን ደግሞ አፍልቶ መጠቀም፣ ምግብን አብስሎ መመገብ፣ የግል እና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ እና ከአላስፈላጊ ንክኪ መቆጠብ የበሽታው መከላከያ እንደሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።