ተመድ በመካከለኛው ምስራቅ የሚስተዋለው አደገኛ የበቀል አዙሪት እንዲቆም አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን አደገኛ የበቀል አዙሪት ማስቆም አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
የዋና ፀሐፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በሰጡት መግለጫ፤ ዋና ፀሐፊው በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን አደገኛ የበቀል አዙሪት ለማስቆም ጊዜው አሁን ነው ማለታቸውን አንስተዋል።
ዋና ፀሐፊው ማንኛውንም የበቀል እርምጃ እንደሚያወግዙ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እንቅስቃሴው ተስፋፍቶ በቀጣናው እና በሌሎችም ላይ አስከፊ መዘዝ እንዳያስከትል በጋራ እንዲከላከል ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
ጉቴሬዝ በትናንትናው ዕለት ሁኔታው ሁሉን አቀፍ ቀጣናዊ ግጭት ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውንም አንስተዋል።
ሊመጣ ስለሚችለው መዘዝ በማስጠንቀቅ የበቀል አዙሪት ውስጥ ከመግባት እንዲታቀቡ ጠይቀዋል፡፡
የተሳሳተ ስሌትና ግንኙነት ወዳልታሰበና ወደ ለየለት ቀጣናዊ ግጭት ሊያመራ ይችላል ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ይህም ለሁሉም ተሳታፊ አካላት እና ለተቀረው ዓለም ከባድ ይሆናል ማለታቸውንም አመላክተዋል።
ጉቴሬዝ ኢራን በደማስቆ የሚገኘው ቆንስላዋ ላይ ለደረሰው የአየር ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ በማድረግ ቅዳሜ ዕለት የወሰደችውን የበቀል እርምጃም ማውገዛችውን ቃል አቀባዩዋ መግለጻቸውን ሻፋቅ ኒውስ ዘግቧል።