በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከተከሰተው የጎርፍ አደጋ በኋላ ፍርስራሹን የማጽዳት ስራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉ ከተከሰተው የጎርፍ አደጋ በኋላ ፍርስራሹን የማጽዳት ስራ ተጀምሯል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ የጎርፍ አደጋው የአንድ ሰው ህይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆን፥ የመኖሪያ ቤቶችና ንግድ ቤቶች በከባድ አውሎ ንፋስ ጉዳት ደርሶባቸዋልም ተብሏል፡፡
አደጋው ከተከሰተ ከሰዓታት በኋላ የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች በመላ ሀገሪቱ በጎርፍ የተጥለቀለቁ መንገዶችን ለማጽዳት ውሃውን በፍሳሽ ማስወገጃ ለማፍሰስ ሲጥሩ እንደነበርም ነው የተነሳው፡፡
ሆኖም እስካሁን የጉዳቱ መጠን አልተገለጸም።
የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ሪከርድ የሆነ የዝናብ መጠን ማሳየቱንም ነው የሀገሪቱ ሚቲዎሮሎጂ ማዕከል የገለጸው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከባድ ዝናብን ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ በቂ የውኃ ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቶች የሌሏት ሲሆን፤ ይህም የሆነው ብዙውን ጊዜ ዝናብ በዓመት ጥቂት ጊዜ ብቻ የሚጥል በመሆኑ ነው፡፡
በዚህም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዝናብ መጠንን ለመጨመር በተደጋጋሚ የደመና ማከማቸት ስራዎችን ያደርጋሉ መባሉን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ፍርስራሾችን ከመንገድ ላይ ሲያፀዱ ትምህርት ቤቶች ዛሬ በኦንላይን ትምህርት መስጠት እንዲቀጥሉ መንግስት አዟል ነው የተባለው፡፡
የዱባይ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ በበኩሉ፥ የጣለው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሮ በረራዎች በመዘግየታቸው እና በመቀየራቸው በዱባይ ያሉ መንገደኞች ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዳይሄዱ መክሯል።