በአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለገበያ ከቀረበ ምርት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስምንት ወራት በአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረበ ምርት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ተኪ ምርቶችን በማምረት ለውጭ ምንዛሬ ይወጣ የነበረን ከ19 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ማዳን መቻሉን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ዘመን ጁነዲን ተናግረዋል፡፡
በፓርኩ አካባቢ ከሚገኙ ነዋሪዎችና የሀገር ውስጥ አምራቾች ጋር ግብዓት ለማቅረብ በተፈጠረ የገበያ ትስስርም ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ከ1 ሺህ 500 በላይ ዜጎች በፓርኩ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ሦስት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በሴራሚክና እንጨት ሥራ ተሰማርተው በማምረት ላይ እንደሚገኙም አመላክተዋል፡፡