የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከአፍሪካ ኅብረት ንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከአፍሪካ ኅብረት ንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ ጋር አብሮ ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡
ውይይቱም ግብርናን እና ኢንዱስትሪን ተመጋጋቢ አድርጎ በመሥራት ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአኅጉር ደረጃ ተቀናጅቶ መሥራቱ ጥሩ ተሞክሮዎችን ከመለዋወጥ ባሻገር ለአፍሪካ ኢንዱስትሪ ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አቶ መላኩ በውይይታቸው ላይ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ተቋማቸው የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ ለመደገፍና በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይም የአፍሪካ ኅብረት በሚያካሂደው የኢንዱስትሪ ሣምንት ዐውደ-ርዕይ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ግብዣ አቅርበዋል።