በመዲናዋ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የጋራ ግብረ ሃይሉ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ ህዝብ የታደመበት እና በአዲስ አበባ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በስኬት እና በሰላም እንዲጠናቅ ለማስቻል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ከአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የታደሙበት የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን ግብር ኃይሉ አስታውቋል፡፡
በተያዘው ዓመት በርካታ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት የታደመባቸው ልዩ ልዩ የአደባባይ ሁነቶች ሃይማኖታዊ በዓላት እና ስፖርታዊ ዝግጅቶች በሰላም መከናወናቸው የሚታወስ ነው፡፡
ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የተለመደውን ትብብር በማድረጉና በተለይ መላው የፀጥታ አካላት ድካማቸውን ተቋቁመው ሃላፊነታቸው በትጋት በመወጣታቸው በ2016 ዓ.ም መዲናዋ ያስተናገደቻቸው አበይት ኩነቶቹ ፍፁም ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው እና በርካታ ህዝብ የታደመበት ሰልፍም በሰላም እንደጠተናቀቀ ግብረ ኃይሉ ማስታወቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ሰልፉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር እንዲሁም ሃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ መላው የፀጥታ አካላት አመራርና አባላት የጋራ ግብረ ሃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡