እስራኤል ወደ ጋዛ የእርዳታ ማስተላለፊያ አዲስ መስመሮችን ልትከፍት መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ተጨማሪ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ማድረስ የሚያስችሉ ሁለት መስመሮች እንዲከፈቱ መወሰኗን ገልጻለች።
በሰሜን ጋዛ የሚገኘው የኤረዝ መግቢያ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚከፈት የተገለጸ ሲሆን፤ የአሽዶድ ወደብም ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ክፍት ይደረጋል ተብሏል።
ከዮርዳኖስ በተጨማሪ በከረም ሻሎም መሻገሪያ በኩል እርዳታ እንዲገባ እንደሚፈቀድ ተመላክቷል፡፡
ውሳኔው የተላለፈው በጋዛ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት የእርዳታ ሰራተኞች መገደላቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ከተነጋገሩ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል።
እስራኤል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ድርጊቱን “ከባድ ስህተት” ያለች ሲሆን፤ በገለልተኛ አካል ምርመራ ለማድረግም ቃል መግባቷ ተነግሯል።
እስራኤል የአሜሪካን ድጋፍ ለማስቀጠል ከፈለገች በንፁሃን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እና ሰብአዊ ስቃይ ለመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ አለባት ሲሉም ባይደን ለኔታንያሁ ማስገንዘባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።