Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር መሥራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሊሳ ሮሰን እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በባንኩ ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሥራ ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም÷ የፕላስቲክ ገመድ አምራቹ አሁን ኢንጂነሪንግ እና ኤቲኤም ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራች ኢንተርፕራይዞችን መመልከታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

የጉብኝቱ ዓላማ ከባንኩ በተገኘ ብድር በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመሰማራት የሥራ ዕድል የፈጠሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት በመመልከት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ ዜጎች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ሊሳ ሮሰን በበኩላቸው÷ በጉብኝታቸው ባዩዋቸው እንቅስቃሴዎች መደሰታቸውን እና የተመለከቷቸው አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣመ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓለም ባንክም በቀጣይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.