ፕሬዚዳንት ፑቲን የሰብዓዊነትና የምህረት ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞስኮ ከደረሰው የሽብር ጥቃት በኋላ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሰብአዊነት እና የምህረት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክሮከስ የከተማ አዳራሽ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ባደረጉት ንግግር የሰብዓዊነት እና የምህረት አስተሳሰቦች ልዩ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በሞስኮ የህግ አውጭዎች በአሸባሪዎቹ ላይ የሞት ቅጣት ለመወሰን ህጉን ወደነበረበት ለመመለስ ክርክር መግጠማቸውን ተከትሎ ነው።
በክሬምሊን ለወጣት አርቲስቶች እና አስተማሪዎች ክብር ለመስጠት በተዘጋጀ ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፤ ባለፈው አርብ በሞስኮ የሙዚቃ ድግስ ላይ በደረሰው የሽብር ጥቃት ከ130 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አንስተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰብአዊነት እና የምህረት እሴቶች ላይ መታመን አሁን ለእኛ በጣም ጠቃሚው ነገር ነው ብለዋል፡፡
ወትሮም በአንድነት እና በጥንካሬ ለመቆም ቆራጥ ውሳኔ ያለን ህዝቦች ነን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የጥቃቱ አድራሾች የተጎዱትን በመርዳት አንድ እንድንሆን አድርገውናል ሲሉ መናገራቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡
የፑቲን አስተያየት ክሮከስ ከተማን በደም ያጠቡትና ወደ ዩክሬን ለመሸሽ ሲሞክሩ በተያዙት ተጠርጣሪዎች ላይ የሞት ፍርድ እንዲሰጥ የሕግ አውጭዎች እና ህዝቡ የሚያቀርቡትን ጥሪ ቀለል ለማድረግ ታስቧል የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።