ሩሲያ የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል ባለቻቸው አራት ግለሰቦች ላይ ክስ መሰረተች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፍርድ ቤት ከቀናት በፊት በሞስኮ አቅራቢያ ክሮከስ ከተማ የኮንሰርት አዳራሽ ውስጥ በተፈፀመውን የሽብር ጥቃት እንዳለበት የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ላይ ክስ መስርቷል፡፡
ተጠርጣሪዎች ዳሌርዦን ሚርዞዬቭ፣ ሳይዳክራሚ ሙሮዳሊ፣ ሻምሲዲን ፋሪዱኒ እና ሙሐመድ ሶቢር ፋይዞቭ የተባሉ ሲሆን የሩሲያ ፍርድ ቤተ በግለሰቦቹ ላይ የሽብር ድርጊት በመፈጸም ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታውቋል።
ግለሰቦቹ የታጃኪስታን እና የሩሲያ ዜግነት እንዳላቸው የገለጸው ፍርድ ቤቱ÷ ከፍርድ በፊት እስከ ፈረንጆቹ ሰኔ 22 ድረስ በእስር እንደሚቆዩ አስታውቋል፡፡
በሞስኮ አቅራቢያ ክሮከስ ከተማ ኮንሰርት አዳራሽ ውስጥ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት በርካታ ሩሲያውያን ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
ከሽብር ጥቃቱ ጋር በተያያዘ አይኤስአይኤስ (ISIS) የተባለው የሽብር ቡድን ሃላፊነቱን ቢወስድም የሩሲያ ባለስልጣናት ግን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የዩክሬን እጅ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በሰጡት መግለጫ÷ ጥቃት አድራሾቹ በዩክሬን ሲታገዙ እንደነበር እና አሸባሪዎች ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ ድንበር አቋርጠው ወደ ዩክሬን እንዲገቡ ሽፋን ስትሰጥ ነበር ብለዋል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ከ100 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች በሰፈሩበት እና በበርካታ ፈንጂዎች በታጠረው ድንበር አሸባሪዎቹ ወደ ዩክሬን ሊያልፉ ነበር ማለት እርባና ቢስ ክስ ነው ስትል ማስተባበሏን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡