የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሰማራት አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ኢኮኖሚ ማደግ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
መድረኩ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ማበረታቻዎችን ለሀገር ውስጥ ባለሀብቱ በማስተዋወቅ ለዘርፉ ዕድገት የሚያበረክተውን ተሳትፎና ሚና ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በሚኒስቴሩ የግብዓትና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ እንዳሉት፥ ዘርፉ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሽግግር ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
በዚህም ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሰማራት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ ስኬትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲመጣ “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ወደ ተግባር ገብቶ በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በውይይቱ የኢትዮጵያን የአምራች ኢንዱስትሪ ታሪካዊ ዳራና አሁናዊ የዘርፉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ መልካም አጋጣሚዎችና የማበረታቻ ስርዓቶችን የሚያሳይ ሰነድ መቅረቡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።