Fana: At a Speed of Life!

7 ሺህ 580 ጥይቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ጎንደር ከተማ ለማስገባት የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሸከርካሪ አካል ውስጥ ደብቆ ወደ ጎንደር ከተማ ለማስገባት የተሞከረ 7 ሺህ 580 የክላሽና የብሬል ጥይቶችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በጎንደር ከተማ 1ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ሰጠኝ ጌታሁን እንደተናገሩት፤ ተጠርጣሪዎቹ በድብቅ ከያዙት ጥይት ጋር በቁጥጥር ስራ የዋሉት ዛሬ ጠዋት ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው።

በህብረተሰቡ ጥቆማ መነሻነት የፀጥታ መዋቅሩ ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ በከተማው መግቢያ ከሚገኘው ወለቃ የፍተሻ ኬላ ላይ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-08204 አማ በሆነ ቶዮታ ፒክአፕ ተሽከርካሪ በውስጥ አካሉ በተዘጋጀ ድብቅ ስፍራ ውስጥ 7 ሺህ 500 የክላሽ እንዲሁም 80 የብሬል ጥይት እንደተገኘ አስታውቀዋል።

በዚህም የመኪናው አሽከርካሪና ሌላ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ረዳት ኢንስፔክተር ሰጠኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለግጭትና ለወንጀል ድርጊቶች መስፋፋት በር የሚከፍት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.