በተደጋጋሚ በጆሮ ማዳመጫ ሙዚቃ ስትሰማ የነበረች ወጣት ለመስማት ችግር ተዳረገች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና ሻንዶንግ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ወጣት ዋንግ ምሽት ወደ መኝታዋ ስትሄድ ሙዚቃ በጆሮ ማዳመጫ (Earphone) አማካኝነት መስማትን ልማዷ አድርጋለች።
ዋንግ ¬- የጆሮ ማዳመጫ – ሙዚቃ የሚለያዩ አይደሉም፤ ዋንግ ሌሊቱን ሙሉ የጆሮ ማዳመጫዋን ከጆሮዋ ሳትነቅል ሙዚቃ ታዳምጣለች።
የጆሮ ማዳመጫውን ሳትነቅል ሙዚቃ እየሰማች በተደጋጋሚ በዚያው እንቅልፍ ይወስዳታል።
ይህ የዋንግ ልማድ የኋላ ኋላ ጣጣ አምጥቶባት ለመስማት ችግር ተጋልጣለች።
ብዙ ጊዜ አለቃዋ በስብሰባዎች ላይ በሹክሹክታ ሲነግራት ምን እንዳላት ለመረዳት ትቸገር እንደነበር የገለጸችው ወጣቷ ሁኔታው በመጨረሻም በስራ ላይ ችግር እንዳይፈጥርባ ትጨነቅ እንደነበር ትናገራለች።
ጉዳዩ እረፍት የነሳት ወጣትም የገጠማትን ችግር ለማወቅና ምርመራ ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ትሄዳለች፡፡
በተደረገላት ጥልቅ ምርመራም ወጣቷ በግራ ጆሮዋ ዘላቂ የሆነ የመስማት ችግር እንዳጋጠማት ታረጋግጣለች፡፡
የሆነ የአካል ጉዳት ገጥሟት አሊያም ጆሮዎቿ ለረጅም ጊዜ ለከፍተኛ ድምፅ ተጋልጠው ከሆነ የተጠየቀችው ዋንግ የምታስታውሰው ነገር በየምሽቱ በጆሮ ማዳመጫዋ ሙዚቃ ማዳመጧን ብቻ እንደሆነ ተናግራለች።
ኮሌጅ ሳለች ሙዚቃ እያዳመጠች መተኛት እንደምትወድ የገለፀችው ወጣት ሌሊቱን ሙሉ ማዳመጫውን ከጆሮዋ ሳታነሳ የመተኛት ልምድ ሱስ ሆኖባት ለሁለት ዓመታት ያክል በዚሁ መልክ መቆየቷን አብራርታለች፡፡
በሆስፒታሉ ከአንገት በላይ ህክምና ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ሊ ታኦ÷ የዋንግ የመስማት ችግር መንስኤ በየምሽቱ ሙዚቃ እያዳመጠች ማደሯ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድምፁ ከፍተኛ ባይሆንም ጆሮዎች ለረጅም ጊዜ ለማያቋርጥ ድምፅ የሚጋለጡ ከሆነ ለመስማት እክል ሊዳረጉ ይችላሉ ማለታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
ዋንግ እንደ ዕድል ሆኖ በማያቋርጥ ተደጋጋሚ ድምፅ የተጎዳው የግራ ጆሮዋ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተሩ ጉዳቱ በማዳመጫ መርጃ መሣሪያ ሊታገዝ እንደሚችል አመላክተዋል።
ከአራት ዓመት በፊት አንድ ታይዋናዊ ሙዚቃ እያዳመጠ የጆሮ ማዳመጫውን ሳያነሳ ተኝቶ ሲነቃ አንድ ጆሮው የመስማት አቅሙን አጥቶ ማግኘቱን የሚገልፅ ተመሳሳይ ታሪክ ማቅረቡንም ዘገባው አስታውሷል፡፡