ለሆርቲካልቸር ኢንቨስመንት ትኩረት በመሰጠቱ የግብርና ወጪ ምርቶች ስብጥር አድጓል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ለሆርቲካልቸር ኢንቨስመንት ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የግብርና ወጪ ምርቶች ስብጥር እያደገ መምጣቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በተለይም የአበባ ወጪ ንግድ ከቡና በመቀጠል ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት 2ኛ ደረጃ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ሰባት ዓመታት እያስገኘ ከነበረው 272 ሚሊየን ዶላር በአሁኑ ወቅት ከ658 ሚሊየን ዶላር በላይ በማደግ ተስፋ የሚጣልበት ዘርፍ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ሀገራችን በአበባ ወጪ ንግድ ከዓለም 5ኛ ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃ እንድትይዝ አስችሏል ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችንና ምቹ አጋጣሚዎችን ያነሱ ሲሆን÷ በሚኒስቴሩ በኩል በተሰጠው ምላሽ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ለመደገፍና ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል፡፡