የሜሲን ስም በመጥራት ከሃማስ እገታ የተረፉት የ90 ዓመት አዛውንት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ90 ዓመቷ አዛውንት የሊዮኔል ሜሲን ስም በመጥራት ከሃማስ እገታ መትረፋቸው መሰማቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈፀመበት በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ዕለት ነገሩ የተፈጸመው።
በዕድሜ የገፉት የ90 ዓመቷ አዛውንት ኤስተር ኩኒዮ ቤታቸው ውስጥ ከተቀመጡበት የሃማስ አጋቾች በድንገት ይገቡና የእገታ አደጋ ላይ ይወድቃሉ።
ከስምንት ቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩት አዛውንቷ በሃማስ አጋቾች ታግተው ወደ ጋዛ እንዲሄዱ በሰርጎ ገብ የሃማስ አጋቾች ይነገራቸዋል፡፡
ነገር ግን አዛውንቷ በሰጡት ምላሽ የሃማስ ታጣቂዎችን ሀሳብ ማስቀየሩን ጎል ዶት ኮም ዘግቧል።
በወቅቱ ቤተሰቦችሽ የት ናቸው ብለው ካፋጠጧቸው አጋቾች ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡት አዛውንቷ “አይሁዳዊ ብቻ አይደለሁም አርጀንቲናውዊም ነኝ፣ ኳስ በጣም እወዳለሁ፤ የሊዮኔል ሜሲ አድናቂም ነኝ” በማለት ያስረዳሉ።
የሜሲ አድናቂ የሆነው አጋችም በዚህ ይደሰትና አዛውቷን ከማገት ይልቅ አብሯቸው ፎቶ ይነሳል፤ በዚህም በመነሳት እርሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ሳያግት ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥቶ ሊሄድ ችሏል።
አዛውንቷ÷ የሃማስ ታጣቂዎች ወደ ቤቴ ሲገቡ አረብኛ ቋንቋ እንደማልችል፣ ኢብራይስጥም ትንሽ ትንሽ እንደማወራ፣ ይልቁንም አርጀንቲናዊ እንደሆንኩ እና ስፓኒሽኛ እንደማወራ ነግርኳቸው ሲሉ ትናንት ለማርካ ገልጸዋል።
አጋቹ አርጀንቲና ምንድን ነው ብሎ ጠየቀኝ፤ ኳስ ታያለህ? አርጀንቲና የሊዮኔል ሜሲ ሀገር ነው ብዬ መለስኩለት፤ እሱም ሜሲን እንደሚወደው ነግሮኝ ጠመንጃውን ትከሻየ ላይ አድርጎ አብረን ፎቶ ተነስተን ሰላምታ ሰጥቶኝ ሄደ በማለት ያጋጠማቸውን ሁኔታ አብራርተዋል።
ከማርካ ዘገባ በኋላ በስፋት የተሰራጨውን ይህን ክስተት በተመለከተ አርጀንቲናዊው የኢንትር ሚያሚ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ እስካሁን ያለው ነገር የለም ተብሏል፡፡