አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ትዕግስት አሰፋ በለንደን ማራቶን ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና የወቅቱ የሴቶች ማራቶን ክበረ ወሰን ባለቤት ትዕግስት አሰፋ በ2024 የለንደን ማራቶን ውድድር እንደሚሳተፉ የለንደን ማራቶን አዘጋጅ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የ41 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በ2023ቱ የቫሌንሲያ ማራቶን 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ9 ሰከንድ በመግባት በአንጋፋ ዕድሜ ዘርፍ አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቡ ይታወሳል።
አትሌት ቀነኒሳ በወንዶቹ ዘርፍ በታሪክ የማራቶን ሶስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ከቀነኒሳ በተጨማሪ የወቅቱ የኒውዮርክ ሲቲ ማራቶን አሸናፊ ታምራት ቶላ እና በታሪክ የማራቶን 7ኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሞስነት ገረመው በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡
በሴቶች ደግሞ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት 11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት የወቅቱ የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ እንደምትሳተፍ አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
አትሌት ትዕግስት ከቀድሞዋ የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኬንያዊቷ ብሪግድ ኮስጌይ፣ በዓለም በርቀቱ 4ኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤቷ ሩት ቼፕንጌቲች እንዲሁም ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ፔሬስ ጄፕቺርችር ከባድ ፉክክር ይጠብቃታል ተብሏል፡፡
በዚሁ ርቀት የ2022 የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው እንደምታሳተፍም ተመላክቷል፡፡
የ2024ቱ የለንደን ማራቶን በፈረንጆቹ የፊታችን ሚያዚያ 21 ቀን የሚካሄድ ይሆናል፡፡