Fana: At a Speed of Life!

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሽንት ስርዓት አካላትን ማለትም (ኩላሊትን፣ የሽንት ፊኛን እና የላይኛውን እና የታችኛውን የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሚያጠቃ የኢንፌክሽን ዓይነት ነው።

ለመሆኑ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ ገብቶ በሚራባበት ጊዜ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የሽንት ስርዓት በተፈጥሮ ባክቴሪያዎችን እንዲያስወግድ የተሰራ ቢሆንም አንዳንዴ ተፈጥሮዓዊው መከላከያ መንገድ አሰራሩን በማሽነፍ ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነት ገብተው በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ።

በተፈጥሮ በብልት አቀማመጥ የተነሳ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የተጋለጡ ናቸው፡፡

በዚህም የግብረ ስጋ ግንኙነት ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሴቶችን በተለይ የበለጠ ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሴቶች በተለይ ባላቸው የሰውነት አቀማመጥ ምክንያት በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት፣ በማህፀን ውስጥ በሚቀመጡ አንዳንድ የወሊድ መከላከያዎች እንዲሁም በሴቶች ማረጥ ጊዜ የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከፍተኛ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ከእዚህም በተጨማሪ የሚከተሉት ሁኔታዎች የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ይጨምራሉ፡፡ እነሱም፡-

ጤናማ ያልሆነ የሽንት ቧንቧ ኖሯቸው የሚወለዱ ህጻናት፣ የሽንት ቧንቧ መደፈን( በኩላሊት ጠጠር ምክንያት)፣የበሽታ መከላከያ ስርዓት መጎዳት( ለምሳሌ በስኳር በሽታ ምክንያት ተፈጥሮአዊው በሽታ መከላከያ ብቃት እንዲቀንስ በማድረግ ለኢንፌክሽኑ ተጋላጭ እንዲሆን ያደርጋል)።

እንዲሁም አርቴፊሻል የሽንት ቱቦ (ካቴተር )የሚጠቀሙ ህመምተኞች፣ የሽንት ፊኛ፣ ፕሮስቴት ወይም የኩላሊት ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሰዎች ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.